+251118132191
contact@mint.gov.et
ለምርምር ተግባራት ምቹ ስነምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ለምርምር ተግባራት ምቹ ስነምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢኖቬቨንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ገለፁ።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ውጤቶች የሆኑ 9 የፓተንትና ሁለት የዩቲሊቲ ሞዴል የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ተረክቧል።
በርክክቡ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር)፣ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ(ፕ/ር)፣ የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ(ፕ/ር )፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የባዮ ኢመርጂንግ ነው።
ለምርምር ልማት ምቹ ስነምህዳር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው አስፈላጊ የህግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን በአለም ላይ በምርምር ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ(ፕ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የባዮ ኢኮኖሚ መሰረት መጣል የሚያስችል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ያገኙት 11 ምርምሮች ከእነዚህ ስራዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን ከማውጣት ባለፈ 435 ምርምሮችን በአለም አቀፍ ጆርናሎች ማሳተም መቻሉን አስረድተዋል።
ምርምር በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተኪ ምርቶች ላይ በማተኮር ምርምር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል እንደሚሉት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዋነኛ መሳሪያ ነው።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምርምር ስራዎች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማግኘት ተኪ ምርቶችን ለማስፋፋትና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማበራከት የሚያግዝ ነውም ብለዋል።
በቀጣይም በአለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የአዕምሯዊ ንብረት መፍጠርና ማስመዝገብ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251118132191
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች