+251118132191

contact@mint.gov.et

Font Awesome Icons
Fixed Header Menu Example

በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ ትብብር የተገነባው ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ተደራሽነት ማዕከል (IAC) ተመረቀ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የኢንፎርሜሽን ማኅበረሰብ ኤጀንሲ (NIA) ጋር በመተባበር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገነባውን ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን አክሰስ ሴንተር (IAC) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመረቀ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር ቤተልሄም ላቀው ማዕከሉ እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ክላውድ ኮምፒውቲንግ ባሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ በማተኮር ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና ለወጣት የፈጠራ ባለቤቶች ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የስልጠና አካባቢን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ አካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዲጂታል መሣሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ሁሉን አቀፍነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ያብራሩት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ፤ ይህም ማንኛውም ዜጋ ከዲጂታል ዘመኑ ተጠቃሚነት ወደ ኋላ እንዳይቀር ለማድረግ ለተያዘው አገራዊ ግብ ትልቅ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ንግግር፣ ማዕከሉ ለፈጠራና ለቴክኖሎጂ እድገት አዳዲስ እድሎችን በመክፈት የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያን የ2030 የዲጂታል ስትራቴጂ ለማሳካትና በ2025 በወጣው የፈጠራ ሥራ (Startup) አዋጅ የታለሙ ግቦችን ለመደገፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ዶ/ር በለጠ በንግግራቸው ገልጸዋል።

ይህ ማዕከል ተራ የኢንተርኔት መገልገያ ሳይሆን፣ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ሳይበር ደህንነት ያሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች የሚተገበሩበትና የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ የልህቀት ማዕከል መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ለደቡብ ኮሪያ መንግስትና ለብሔራዊ መረጃ ማህበረሰብ ኤጀንሲ (NIA) ምስጋና አቅርበው፣ ፕሮጀክቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነትና ኮሪያ በዲጂታል ልማት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ክቡር ካንግ ጁንግ (H.E. Kang Jung, Ambassador of the Republic of Korea) ማዕከሉ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠንና የሁለቱን ሀገራት የሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ አክለውም የኮሪያ መንግሥት የዲጂታል ልማት ተሞክሮውን ለኢትዮጵያ ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ይህ ማዕከል በተለይም ለወጣቶችና ለሥራ ፈጣሪዎች የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት መቅሰሚያ ቁልፍ መድረክ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህንን ማዕከል ለመማር፣ ለመሞከርና ለመሪነት እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል። ማዕከሉን እውን ለማድረግ ለደከሙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለሙያዎችና ለኮሪያውያን አጋሮች እውቅና በመስጠት ፕሮጀክቱ በይፋ ስራ መጀመሩን አብስረዋል።

በብዛት የተጎበኙ

News Card Example

መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ     በ2011 ዓ.ም  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  ተቋቋመ፡፡

የትኩረት መስኮች

  • ምርምር
  • ኢኖቬሽን
  • የቴክኖሎጂ ሽግግር
  • ዲጂታላይዜሽን

ያግኙን

  • ስልክ: +251118132191
  • ኢሜል: contact@mint.gov.et
  • ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et

የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች

Font Awesome Icons

©2024 MINT መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።
ከእርምጃ ወደ ሩጫ