+251118132191
contact@mint.gov.et
ትናንት ምሽት በደቡብ ኢትዮጵያ ሀገራችን ክፍል ሰማይ ላይ ስለተፈጠረው ክስተት ከስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት የተሰጠ ሳይንሳዊ ትንታኔ
በጥር 1 ቀን 2017ዓ.ም. የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት ምሽት በደቡብ ኢትዮጵያ የሀገራችን ክፍል ሰማይ ላይ ስለታየው ክስተት በስፍራው በነበሩ የአይን እማኞች የተነሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መነሻ በማድረግ የክስተቱን መነሻ ባለን መረጃ ለመተንተን ተሞክሯል፡፡
በዚሁ መሰረት እየተቃጠለ ተቆራርጦ ወደ ምድር ሲጓዝ የታየው ቁስ ከሚከተሉት አማራጮች በአንዱ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
1. በሰው ሰራሽ የሰፔስ ቁሶች ምክንያት የተከሰተ
ከህዋ ወደ ምድር ሊወርዱ የሚችሉ ሰው ሰራሽ አካላት Space Derbies ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፤ በዋናነት የአገልግሎት ግዜያቸውን ካጠናቀቁ የሳተላይት ቁርጥራጮች ወይም በስራ ላይ ካሉ ሳተላይቶች ወይም ወደ ህዋ ለማምጠቅ ከሚያገለግሉ ሮኬቶች በቴክኒካዊ ጉድለት የተወሰነ ክፍላቸው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደ መሬት በስበት ኃይል ተምዘግዝጎ የሚመጣበት ክስተት ነው፡፡
እነዚህ ቁርጥራጭ አካላት ወደ መሬት ከባቢ አየር ሲገቡ በሰበቃ ምክንያት እሳት የሚፈጥሩ ሲሆን፤ በረዥሙ ጉዟቸው ፍጥነት እየጨመሩ እዛው ሳሉ ተቃጥለው የሚያልቁ ወይም ውሱን አካላቸው ብቻ ከቃጠሎው ተርፎ መሬት የሚደርሱ ናቸው፡፡
ለዚህ እንደ ማሳያ አድርገን ልናቀርብ የምንችለው የኬንያ ስፔስ ኤጀንሲ ማረጋገጫ የሰጠበትን፤ እ.አ.አ. በታህሳስ 30 ቀን 2024 በኬንያ ሙኩኩ በተባለች የገጠር መንደር የተገኘውን ከህዋ ወደ ምድር እየተቃጠለ የመጣ እና በመንደሯ ያረፈ ሰው ሰራሽ የስፔስ ቁስን ነው፡፡
2.በተፈጥሯዊ የህዋ አካላት ምክንያት የተከሰተ
እንደ አጠቃላይ ከህዋ፤ ከጋላክሲ፤ ከስርዓተ ጸሐይ፣ ከፕላኔቶች እና ከጨረቃዎች አፈጣጠር ጋር ተያይዞ ወደ ፕላኔትነት ሳይቀየሩ የቀሩ አለቶች አስትሮይድ ወይም ኮሜቶች ተብለው ይጠራሉ፡፡
በተለይም እኛ ባለንበት ስርዓተ ፀሐይ ውስጥ በማርስ እና በጁፒተር መካከል እንደ መቀነት በዙሪያው ተጠምጥመው ፀሐይን የሚዞሩ የተለያየ መጠን ያላቸው አስትሮይዶች አሉ፡፡
ምድራችንን ጨምሮ የህዋ አካላት በሙሉ በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆናቸው በሂደቱ በመሬት የስበት ኃይል ተጠልፈው በከባቢ አየራችን ውስጥ ሲዘልቁ እሳት የሚፈጥሩ ሲሆን፤ ከዚያ ተርፈው ወደ መሬት መድረስ የቻሉቱ ሜቲዮራይትስ ሲባሉ፤ የከባቢ አየር ሰበቃ የሚፈጥረውን እሳት መቋቋም ሳይችሉ ተቃጥለው አየር ላይ ሳሉ የሚያልቁት ደግሞ ሜቲዮርስ ይባላሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሜቲዮርስ ክስተት በያዝነው ሳምንት ሊኖር እንደሚችል የአሜሪካው ብሔራዊ የኤሮኖቲክስ እና ስፔስ አስተዳደር (NASA) አስቀድሞ የሰጠውን እ.አ.አ. የ2025 ትንበያ ያመላክታል፡፡
ይህ ትንበያ እ.አ.አ. ከታህሳስ 26 ቀን 2024 እስከ ጥር 16 ቀን 2025ዓ.ም ቁጥራቸው እስከ 200 የሚደርስ Quadrantids ተብለው የሚታወቁት የሜቲዮርስ ስብስብ ወደ ምድራችን ሊመጡ እንደሚችሉ ያመላክታል፡፡
በትንበያው መሰረት ወደ ምድር ሲቀርቡም ደማቅ እና የፈካ ብርሐንን ረዘም ላለ ጊዜ እንደሚያሳዩም ተጠቁሟል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የትኛው እንደሆነ በእርግጠኛነት ለመናገር ከቃጠሎ ተርፎ መሬት የደረሰ ቁስ አካል መገኘት ከፍተኛ ፋይዳ ስላለው፤ ክስተቱ በተፈጠረበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ይህንን መረጃ ካገኙ እንዲያጋሩን በትህትና እንጠይቃለን፡፡
አሁን በደረስንበት ምዕራፍ ለህብረተሰቡ የሚኖረን ምክረ ሀሳብ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. እኛም ሆንን የምንኖርበት ምድር አንዱ የህዋ አካል ስለሆነ፤ በሌሎች የህዋ አካላት ላይ የሚፈጠር ክስተት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ተጽእኖው በምድራችን ላይ ሊያርፍ እንደሚችል መረዳት እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ መውሰድ ላይ ብቻ ማተኮር፤
2. ከተፈጥሯዊም ሆነ ከሰው ሰራሽ አካላት ወደ ምድራችን የሚመጡ ቁሶች በአብዛኛው የከባቢ አየር በሚፈጥረው ሰበቃ ተቃጥለው የሚያልቁ ሲሆን፤ ወደ ምድር የሚደርሱትም ቢሆኑ በአብዛኛው ምድራችንን በሸፈነው የውሃ አካል ወይም የሰው ልጅ በማይኖርባቸው ስፍራዎች ስለሚያርፉ የጎላ ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ተጽዕኖ አያደርሱም፡፡
3. ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከቃጠሎ ተርፎ መሬት የሚደርሰው ቁስ በመጠን አነስተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚጓዝ ያነሰም ቢሆን አካላዊ ጉዳት የማድረስ እድል ስላለው፤ ተመሳሳይ ክስተት በሚኖር ጊዜ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ከአደጋ ሊከላከሉ በሚችሉበት ርቀት፤ አቅጣጫ እና መጠለያ ስር እንዲገኙ እንመክራለን፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251118132191
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች