+251118132191
contact@mint.gov.et
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በትብብር የምታገኛቸውን የቴክኖሎጂ እውቀቶችን መጠቀም የምትችልበት ስነ-ምህዳር ላይ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ባይሳ በዳዳ ገለፁ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት (OSC) ጋር በመተባበር የሚበለፅጉ ፈጠራዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከአለም አቀፍ መድረኮች ጋር ለማጣጣምና አጋርነቶችን ለማጎልበት የሚያስችል ከ28 በላይ አባል ሃገራት የሚሳተፉበት ታላቅ የቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ከህዳር 23-24፣ 2017 ዓ/ም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫው የሰጡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ ሀገራችን ከተለያዩ የቴክኖሎጂ አቅም ካላቸው ከአለም አቀፍ ሀገራት ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠርና ልምድ በመጋራት የኢኮኖሚ ምህዋሩን በአጭር ጊዜ ሊዘውሩ የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትየጵያ ብዙ የወጣት ሀይል አላት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ያለንን የሰው ሀይል በቴክኖሎጂው ዘርፍ በማሰማራት ብቁ ሆኖ ራሱንና ሀገሩን መቀየር የሚችልበትን እውቀት፣ልምድና ትጋትን በመላበስ የሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ተሳታፊና ባለቤት ሆኖ ለመሰለፍ እንዲህ ያሉ ዓውደ ርዕዮች ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ዝግጅቱም በትምህርት እና ክህሎት፣ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ በዘላቂ ትራንስፖርት፣ በንጹህና ተመጣጣኝ ኃይል፣ በዘላቂ ግብርና እና በተቀናጀ ጤና አገልግሎት ዘርፍ ላይ የዓውደ ርዕዩን ጎብኚዎች ሳይጨምር ከሃገር ውጪ ያሉና የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉ ተሳታፊዎች ሲኖሩ፤ 300 የሃገር ውስጥ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ትብብር ድርጅት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ኢትዮጵያ የድርጅቱ መስራች ሀገር ከመሆኗም ባለፈ ቴክኖሎጂን ለማልማትና ለመጠቀም የሰጠችው ትኩረት ከሌሎች አባል ሀገራት ተመራጭ ሆና ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት አስችሏታል ብለዋል፡፡
ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የማይቀርበት መንገድ ነው ያሉት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በዓውደ ርዕዩ የቴክኖሎጂ አልሚዎችን፣ ሳይንቲስቶችን፣ የንግድ ማህበረሰቡን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ የሲቪል ማህበረሰቡን፣ የህዝብ እና የግል ዘርፍ ተዋናዮችን ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት (OSC) አባል ሀገራት እና ከሰፊው አለማቀፍ ደቡባዊ የሚገኝ ህብረተሰብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩ አዳዲስ አገር-በቀል የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽኖች፣ የፓናል ውይይቶች፣ ሃካቶንስ (Hackathons) ውድድሮችና ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251118132191
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች