+251111265737
contact@mint.gov.et
ክብርት ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ ከተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር በሥራ አቅጣጫዎች ላይ ተወያዩ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ በፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1440/2019 አንቀጽ 32 መሠረት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ከሆኑት 6 አስፈፃሚ ተቋማት አመራሮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በሥራ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑት ተቋማት፡-
1. የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን
2. የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን
3. የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲቲዩት
4. የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲቲዩት
5. የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን
6. ብሔራዊ የምርምር ፈንድ እና ምክር ቤት ናቸው።
በውይይቱ ወቅት ክብርት ሚኒስትሯ፤ ተጠሪ ተቋማቱ በአዲሱ አዋጅ አዲስ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የተቋቋሙ፣ ከሌሎች ተጠሪ ዘርፎች ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመጡና ተግባርና ኃላፊነታቸውን ወደ ሌላ ተቋም ያስተላለፉ መሆናቸውን አውስተዋል።
አዲሱን የኢትዮጵያ ግራንድ ስትራቴጂና ለዘርፉ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አኳያ የወደፊት ራዕይን በማስቀመጥ፣ ዲጂታላይዜሽንን በሚፈለገው ግብና ፍጥነት መተግበር እንዲቻል ለአጠቃላይ ዘርፉ አስቻይ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።
መድረኩ ተቋማቱ በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ፣ በቀጣይ ተልዕኮዎች ላይ ለመደጋገፍና ቅንጅት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አቅሞችን ለመለየት ያለመ መሆኑን ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትሯ፤ "ሀገሪቱ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንድትነቃቃና ትልቅ ለውጥ እንደምናመጣ እምነት አለኝ" ብለዋል።
አክለውም የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር መሠረት በማድረግ ከተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከተቋሙ ውጪ ካሉ የሀገር ውስጥና የውጭ አጋሮች ጋር በመሆን የሀገሪቱን ፍላጎት በጠበቀ መልኩ እሴት የሚጨምሩና የዲጂታል አካታችነትን በማጎልበት «ዲጂታል ኢትዮጵያን» እውን የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተጠሪ ተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በየተቋማቸው የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ የሚታዩ የሥራ ተግዳሮቶችንና የቀጣይ ዕቅዶችን አቅርበዋል። በተጨማሪም የሥራ ትስስርን ማጠናከር፣ የመረጃ ልውውጥን ማሻሻልና የተለያዩ ተቋማዊ አቅሞችን ለጋራ ዓላማ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችሉ የትብብር አማራጮችን አንስተዋል።
በተጨማሪም የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮች ተቋማቸው የሚገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ (As-Is Status) የሚዳስስ ሰነድ በተሰጣቸው መመሪያ (Guideline) መሠረት እንዲያዘጋጁ አቅጣጫ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በቀጣይም ሚኒስትሯ በየተቋማቱ በአካል ተገኝተው የመስክ ምልከታና ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል፣ ክፍተቶችን ማረም፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማስፈን፣ አስቻይ ምህዳር መፍጠር፣ ከግራንድ ስትራቴጂው ጋር የተቀዳና የተጣጣመ እይታ መፍጠር እና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ማሻሻል በሚሉ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ውይይቱን አጠናቀዋል።
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251111265737
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች