+251111265737
contact@mint.gov.et
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዲስ ለተሾሙ ሚኒስትር ዴኤታዎች አቀባበል አደረገ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ አዲስ ለተሾሙት ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ ሙሉቀን ቀሬ፣ አቶ ሰለሞን ሶካ እና አቶ ዮዳሄ ዓርዓያስላሴ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገዋል።
በመርሐ ግብሩም የተቋሙን ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራትና የጋራ የስኬት ግቦች አስመልክቶ ከሚኒስትር ዴኤታዎቹና ከተቋሙ የሥራ አመራር ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ የመንግሥትን የልማት አቅጣጫዎችና እሳቤዎች ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር በሚያስችሉ የአፈጻጸም ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነበር።
ክብርት ሚኒስትሯ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን፣ ተወዳዳሪነቷን ለማጎልበትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ይህንን ሚና በብቃት መወጣት ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ በማስገንዘብ፣ ሕዝብና መንግሥት ከዘርፉ ተጨባጭና የሚለካ ውጤት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በማሸጋገር ግልጽነትና ቅልጥፍናን ማሳደግ፣ እንዲሁም የአገልግሎቶችን ተደራሽነትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ሀገራችን የጀመረችውን የዲጂታል ሽግግር ለማፋጠንና በቴክኖሎጂና በፈጠራ ዘርፎች ተወዳዳሪ ለማድረግ በጋራ፣ በትኩረትና በጽናት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአቀባበል መርሐ ግብሩ አዲስ የተሾሙት ሚኒስትር ዴኤታዎችም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ክቡር አቶ ሙሉቀን ቀሬ ተቋሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠንና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። የሰው ኃይሉን በእውቀትና በክህሎት በማብቃት፣ እንዲሁም በአዲስ የሥራ መንፈስና ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ፈጣን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ምርምርን፣ ሳይንስንና ፈጠራን ማጠናከር ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለብልጽግናና ለሀገራዊ ሥልጣኔ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። የመደመር ስትራቴጂን በተግባር በማዋልና የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት በእነዚህ ዘርፎች ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ክቡር አቶ ዮዳሄ ዓርዓያስላሴ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ያበረከተውን አስተዋጽኦ አንስተዋል። በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎችን በትብብር ማጠናከር የዲጂታል ሽግግሩን ለማፋጠንና የፈጠራ ውጤቶችን ለማኅበረሰቡ ተጨባጭ ጥቅም ለማዋል ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በመጨረሻም በክብርት ሚኒስትሯ መሪነት ክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች ከሠራተኞች ጋር በሥራ ገበታቸው ተገናኝተው ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን፣ የተቋሙን የሥራ ክፍሎችና የሥራ መገልገያዎችም ጎብኝተዋል።
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251111265737
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች