+251118132191
contact@mint.gov.et
የ2026 የአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሳምንት በታላቅ ድምቀት ተጠናቀቀ።
በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውና የአህጉሪቱን የብልጽግና ጉዞ ሊያፋጥኑ የሚችሉ የላቁ ስኬቶች የተንፀባረቁበት የ2026 የአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሳምንት፤ አህጉራዊ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የልማት አጋሮችን፣ የግል ዘርፍ መሪዎችንና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን በአንድ ጥላ ስር በማገናኘት የቀጣይ የትብብር አቅጣጫዎች የተመላከቱበት ታላቅ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ መርሃ ግብሩ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ የእውቀት መር ኢኮኖሚ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወት የሚያስችል የለውጥ ጥሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ አፍሪካ የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርታማነትና ወደ ክብር ያለው የሥራ ዕድል የሚቀይር የተቀናጀ ሥርዓት መገንባት እንዳለባት በአፅንኦት ገልፀዋል።
አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ቢሆንም ይህ እምቅ አቅም ወደ እውነተኛ ኃይል ሊቀየር የሚችለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆነ ትምህርት፣ በጠንካራ የምርምር ተቋማት፣ በዘመናዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት እና በዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ ሲደገፍ ብቻ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ባዮቴክኖሎጂ ባሉ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለአህጉሪቱ ሉዓላዊነትና ጽናት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ (AUDA-NEPAD) ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ናርዶስ በቀለ-ቶማስ በበኩላቸው፤ የፈጠራ ስራ ትርጉሙ ከቴክኖሎጂ ግኝት ባለሻገር የተጨባጭ ሰዎችን ህይወት መለወጥና ጠንካራ አህጉራዊ አጋርነትን መፍጠር መሆኑን በመጥቀስ፣ ትኩረታችንም በሀገር በቀል መፍትሄዎችና በስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ላይ ሊሆን እንደሚገባ በፅኑ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ከፍተኛ እውቅና ካገኙ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል የ17 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት መልካም አስራት "Vibrio AI Cholera" የተሰኘና የኮሌራ ወረርሽኝን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ድንቅ የፈጠራ ስራዋን በማቅረብ፣ የአፍሪካ ወጣቶች ለአህጉራዊ ችግሮች መፍትሄ አመንጪ መሪዎች መሆናቸውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር አሳይታለች።
በመጨረሻም የጋምቢያው ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር መሐመድ ቢ. ኤስ. ጃሎውና የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ክቡር ጃካያ ኪክዌቴ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት በተጠናቀቀው በዚህ መድረክ ላይ፣ ስትራቴጂው በመደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ ሰነድ ሆኖ እንዳይቀር የሀገር ውስጥ የምርምርና ልማት ፈንድን በማጠናከርና ሳይንቲስቶችን በመደገፍ አህጉሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ብልጽግናን እንድታረጋግጥ የጋራ ጥሪ ቀርቧል።
በብዛት የተጎበኙ
መንግስት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡
የትኩረት መስኮች
- ምርምር
- ኢኖቬሽን
- የቴክኖሎጂ ሽግግር
- ዲጂታላይዜሽን
ያግኙን
- ስልክ: +251118132191
- ኢሜል: contact@mint.gov.et
- ድረ-ገጽ: www.mint.gov.et
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች